My Blog List

Thursday, July 21, 2016

ወጣትነትና ክርስትና

ክርስትና  በእድሜ፣ በጾታ  እንዲሁም  በትምህርት  ደረጃ  የሚወሰን  ሳይሆን  በየትኛውም  ሁኔታ  ውስጥ ሆነን  የምንመራበት  ሕይወት  ነው፡፡  ‘‘በጊዜውም አለጊዜውም ጽና’’ እንዲል፡፡ 2ኛ  ጢሞ  4፤2  ፡፡ በስጋችንና በነፍሳችን፣ በሃሳባችንና በድርጊታችን፣ በመውጣትና መግባታችን፣ በኑሯችን ሁሉ እግዚአብሔርን የምንፈልግበትና ከእርሱም ጋር ኅብረት የምናደርግበት የተቀደሰ ሕይወት ነው፡፡ ‘‘ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን’’ ተብሎ እንደተጻፈ ክርስትናችን በብርሃን እየኖርንና እየተመላለስን ከአምላካችን ጋር  ኅብረት የምናደርግበትም ነው፡፡ 1ኛ ዮሐ 1፣7፡፡ ወጣትነት  በሰው ልጆች አጠቃላይ ሕይወትና በክርስቲያናዊ ኑሮ ውስጥ ትልቅ  ድርሻ  አለው፤  ምክንቱም  የወጣትነት ዘመን ቢሰሩ የማይደክሙበት፣ ቢሮጡ የሚቀድሙበት፣   ሲያረጁ  የሚጦሩበትን  ሀብትና ንብረት የሚያፈሩበት የእድሜ ክልል በመሆኑ ነው፤ ስለሆነም በክርስትና ሕይወት ውሥጥ ስንኖር ጉዟችን ሁሉ የተሳካ፣ በማስተዋል የሚደረግና እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኝ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ወጣትነታችን ስጋችንንም ሆነ ነፍሳችንን የምንቀድስበት ሕይወት እንዲሆን ጥረት ማድረግ የሁላችንም ድርሻ ነው፡፡ ‘‘ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች፡፡’’ እንደተባለ ወጣትነታችን የማንሰራበት ወቅት ከመድረሱ በፊት ያለ የስራ ክፍለ ጊዜ ነው፡፡ ዮሐ 9፣4፡፡ ‘‘የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ’’ የተባልነውም ወጣትነታችን የጉብዝናችን ወራት ስለሆነ ነፍሳችንንና ስጋችንን ሊጠቅም የሚችል በጎ ስራ እንድንሰራበት ነው፡፡ መክ 12፣1፡፡
የወጣትነት ሕይወት ፈተናዎች
     1.ትእቢት
የወጣትነት  ጊዜ ስጋችን ብርቱና ንቁ የሚሆንበት ወቅት ስለሆነ ብዙውን ጊዜ ሁሉን ነገር ያደረግነውና ማድረግ የምንችለው፣ ሁሉም  ነገር በጥረታችንና በእጃችን ብርታት ብቻ እንደሆነ ልናስብ እንችላለን፡፡ ሁሉም ነገር የራሳችን  ድካም ፣ የስራችን፣ የእውቀታችንና የጥንካሬያችን ውጤት እንደሆነ  እናስባለን፡፡ ይህም በእግዚአብሔር ላይ የሚኖረን መደገፍ እንዲቀንስ ስለሚያደርግ በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንድንዝልና ከእግዚአብሔር ኅብረት እንድንርቅ የሚያደርግ የዲያብሎስ ውጊያ ነው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል የመከረን፡- ‘‘በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችኹ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችኹ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችኹ በእምነት ጸንታችኹ ተቃወሙት።’’ 1ኛ ጴጥ 5፣8፡፡ በእግዚአብሔር አለመደገፍና ሁሉን ለራስ አቅም መተው ክርስትናችንን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚመራ ታላቅ ውጊያ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሰው እጁና ብርታቱ ብቻውን የሚፈለገውን ውጤት እንደሚያመጣ አያስብም፤ ከዚህ ይልቅ ሁልጊዜም ይህን ቃል ያስባል፡- ‘‘በልብኽም፦ ጕልበቴ የእጄም ብርታት ይህን ሀብት አመጣልኝ እንዳትል። ነገር ግን፥ ዛሬ እንደ ኾነ ለአባቶችኽ የማለውን ቃል ኪዳን ያጸና ዘንድ፥ ሀብት ለማከማቸት እርሱ ጕልበት ሰጥቶኻልና፥ አምላክኽን እግዚአብሔርን ዐስብ።’’ ዘዳ 8፣17-18፡፡ ስለሆነም አንድ ክርስቲያናዊ ወጣት ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ ተስፋ የሚያደርገው፣ የሚደገፍበትና የሚታመንበት ኃይል ሊኖረው አይገባም፡፡
   2. ችኩልነት
ችኩልነት  ሌላው  የወጣቶች  የክርስትና ሕይወት ፈተና  ወይም  እንቅፋት  ሲሆን  ነገሮችን ተረጋግቶ ባለማሰብና ባለማስተዋል ወደተግባር  እንድንገባ የሚገፋን ኃይል ነው፡፡ ሁሉም ነገር እኛ በምንፈልገው ልክ፣ መጠንና ፍጥነት ሆኖ ካላየን የምንልበት የጥድፊያ ሕግ ነው፡፡ ይህም ደግሞ ከእውነቱ ዓለም ሕግ ጋር ስለሚጣረስ ባሰብነው ልክ ሆኖ ሳናገኘው ስንቀር ተስፋ እንድንቆርጥ፣ ለሕይወት ያለን ግምት እንዲቀንስ፣ ደስተኞች እንዳንሆን፣ ከእውነታው ጋር እንድንጣላና በእግዚአብሔርም ላይ ያለን መደገፍ እንዲቀንስ ያደርገናል፡፡ እንደ ክርስቲያን ልናደርገው የሚገባን ነገር ቢኖር ሁሉም የሚሆንበትና የሚከናወንበት የራሱ የሆነ የጊዜ ዑደት እንዳለው ተረድተን የድርሻችንን እየተወጣን ሌላውን ለጊዜ ጌታ ለእግዚአብሔር መተውና እርሱንም መጠበቅ ነው፡፡ መቸኮላችን ባለን ነገር እንዳናመሰግንና ደስተኞች እንዳንሆን ስለሚያደርገን ቁጡዎችና ተረጋግተን ማስተዋል የማንችል እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ‘‘በነፍስኽ ለቍጣ ችኵል አትኹን ቍጣ በሰነፍ ብብት ያርፋልና።’’ መክ 7፣9፡፡

   3.  አለማስተዋል
ነገሮችን ተረጋግቶ ማስተዋል መቻል የበሳል ክርስቲያን መገለጫ ነው፡፡ “ገንዘብ  በሃያ  አመት  ሌብ  በአርባ  አመት”  የሚባለውም ብዙ ጊዜ ወጣትነት ከማስተዋልና ከመረጋጋት ሕይወት ሲርቅ ስለሚታይ ነው፡፡ ነገሮችን ተረጋግቶ ማስተዋል አለመቻል በመንፈሳዊ ሕይወታችንም ሆነ በተግባረ ስጋችን መጠቀም ያለብንን ያህል እንዳንጠቀም፣ ከእግዚአብሔርም ጸጋንና በረከትን እንዳንቀበል እንቅፋት ይሆንብናል፡፡ ማስተዋል ካልቻልን ምን ማድረግና ምን አለማድረግ እንዳለብን መለየት ያቅተናል፣ ስለሆነም ሕይወታችን የእግዚአብሔር ሃሳብና ምክር ያልተገለጠበት፣ ከእግዚአብሔር ሃሳብ በእጅጉ የራቀ፣ ከዘላለማዊ መንግስቱም በአፍኣ/ውጪ ይሆናል፡፡ “በእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ኀይል አለ፤ ለርሱ ምክርና ማስተዋል አለው።” ተብሎ እንደተጻፈ ከእግዚአብሔር የሆነውን ይህን ጥበብ፣ ኀይል፣ ምክርና ማስተዋል ገንዘብ ለማድረግ መጣር ሕይወታችንን የተቃና ያደርግልናል፡፡ ኢዮ 12፣13፡፡ በምድር ላይ የምንኖረው ሕይወታችን ዝም ብለን በአጋጣሚ የምንኖረው ሳይሆን በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ሃሳብና ምክር የሆነም ስለሆነ ራሳችንን ለዚህ ዘላለማዊ ፈቃድና ሃሳብ በማስገዛት እርሱን ደስ ለማሰኘት የምንጥርበት፣ በማስተዋልና በጥበብ የምንኖረው ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ “በጌታችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት እደጉ”  ስለተባልን ክርስትናችን ከክርስቶስ የሆነውን ጸጋ፣ ዕውቀትና ማስተዋል በመፈለግ የምናድግበት ሕይወት ነው፡፡   2ኛ ጴጥ 3፡18፡፡
   4. ለዘመናዊነት ያለን የተዛባ ዕይታ
ዘመናዊነት በጣም ብዙ የሚጠቅሙ ነገሮች አንዳሉት የሚካድ አይደለም፡፡ ዘመናዊነት የጥበብ መንፈሳዊና ጥበብ ስጋዊ ውጤት በመሆኑ ብዙዎቹ በዘመናዊነት ውስጥ የተፈጠሩ የቴክኖሎጂ ግኝቶች የሰውን ልጅ  የቀን  ተቀን  ስራዎችን  በማገዝና በማቀላጠፍ ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖ አላቸው፡፡ ጥብብ የእግዚአብሔር ስጦታ በመሆኑ የዘመን ግኝቶች ለበጎ ተግባራት እስከዋሉና እግዚአብሔርን በመፍራት እስከተጠቀምንባቸው ድረስ ምንም ጉዳት አይኖራቸውም፡፡ ስለሆነም “ሃይማኖት  አንደ  አባቶቻችን  ጥበብ  እንደጊዜያችን”  እንላለን፡፡ የዘመን ግኝቶችን ለእግዚአብሔር አገልግሎትና ለሰው ልጆች ሁሉ ጥቅም፣ ለፍቅርና ለበጎ ስራ መጠቀም የክርስቲያኖች ሁሉ ኃላፊነት ነው፡፡ “ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ”  የተባልነው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በእግዚአብሔር ፍርሐትና በመንፈሳዊ ጥበብ እንድንጠቀምባቸውም ነው፡፡ ኤፌ 5፣6፡፡ ዘመንን መዋጀት ማለት በዘመን ለውጥ ውስጥ በለውጡ ተጽዕኖ ውስጥ ሳንሆን የእግዚአብሔርን ሃሳብና ፈቃዱንም ማገልገል መቻል ማለት ነው፡፡
ዘመናዊነት ካመጠቸው ግኝቶች መካከል ማህበራዊ ሚዲያዎች በወጣቶች ሕይወት ውስጥ ያላቸውን ተጽዕኖ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ብንመለከት ፌስቡክና መሰል ማኅበራዊ ሚዲያዎች ዓለማችንን የአንድ መንደር ያህል ማቀራረብ የቻሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች/ግኝቶች ናቸው፡፡ በተለያዩ የምድራችን ክፍሎች ወስጥ የሚገኙ ሰዎች ርቀት ሳይገድባቸውና ሳይወስናቸው ከአንደኛው  የዓለማችን ጫፍ ወደሌላኛው የዓለማችን ጫፍ  እነዚህን የመገናኛ መረቦች ተጠቅመው  መልእክቶችንና  መረጃዎችን ይለዋወጣሉ፣ ሃሳቦቻቸውን ያስተላልፋሉ፡፡ ነገር  ግን  እነዚህን  የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሁሉም ወጣቶች ለበጎ ነገርና ሰዎችን ሁሉ ሊጠቅሙ በሚችሉበት ሁኔታ ይጠቀሙባቸዋል ማለት አይደለም፡፡ የማይረባ ቧልትን ለማስተላለፍ፣ ከሩካቤ ጋር የተገናኙ ምስሎችንና ፊልሞችን ለማሳየት፣ የማኅበረሰብን ጤናማ ግንኙነቶችና እሴቶቻችን የሚፃረሩ ሃሳቦችን ለማስተላለፍ፣ ዘረኝነትንና መለያየትን ለማስረጽ የሚጠቀሙባቸው ወጣቶች ቁጥር ትንሽ የሚባል አይደለም፡፡  “እንግዲህ ማንም ራሱን ከነዚህ ቢያነጻ፥ ለክብር የሚኾን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ዅሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይኾናል።” ተብሎ እንደተጻፈ የእግዚአብሔር የሆኑ ወጣቶች ራሳቸውን ለወደዳቸውና ለሞተላቸው ጌታ አሳልፈው የሰጡ ስለሆኑ የሚያደርጉት ማናቸውም ነገር የእግዚአብሔር ክብር የሚገለጥበትና በዙሪያቸው ያሉ ሰዎችንም የክርስቶስን ፍቅር ወደማወቅ የሚያደርስ ነው፡፡ 2ኛጢሞ2፣21፡፡ “በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችኹ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ።” ስለተባልን ማኅበራዊ ሚዲያዎች ግንኙነቶቻችንን የሚያሳልጡና የሚያግዙ እንጂ ሱስ ሆነውብን ለክርስቶስ ያለንን የተቀደሰ ሕይወት የሚያሳጡን ሊሆኑ አይገባም፡፡ ገላ 5፣1፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በራሳቸው ኃጢአት ባይሆኑም በአጠቃቀማችን ላይ በምንፈጥራቸው ስህተቶች ለኃጢአቶቻችን ምክንያት ሊሆኑ ግን ይችላሉ፡፡ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን አይጠቅምም። ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሰለጥንብኝም” ተብሎ እንደተጻፈ ይህ የምንኖረው የምድር ኑሯችን የእኛ ሳይሆን ለክርስቶስ ብለን የምንኖረው ስለሆነ ሁሉን ለክርስቶስ እንቀድሳለን እንጂ ለዓለሙና ለክፋቱ አንሸነፍም፡፡ 1ኛ ቆሮ 6፣12፡፡ ራሱን ለእግዚአብሔር እንደሚቀድስና ክርስቶስን ደስ ለማሰኘት እንደሚጥር ሰው ክርስቲያኖች ሁሉን ለጌታ ክብር ያውሉታል እንጂ በክፋቱ አይተባበሩም፡፡ “እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” 1ኛ ቆሮ 10፣31 ስለተባልን ክርስቲያን ወጣቶች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ሰላምን ለማውራት፣ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለመጎብኘትና ፍቅርን ለማብዛት፣ የክርስቶስን በጎነት ለማውራት፣ የእግዚአብሔርን መንግስት በሰው ልጆች ሁሉ ፊት ለማስፋት ልንዋጃቸው ያስፈልገናል፡፡
    5. ቸልተኝነት
በምድር ላይ ስንኖር የእግዚአብሔርን ፈቃድና ሃሳብ እየፈጸምን እንደሆነ እናምናለን፡፡ የምድር ላይ ኑሯችን በአጋጣሚ፣ ዝም ብለን፤ በዘፈቀደ የምንኖረው ሳይሆን እግዚአብሔር ከዘመናት አስቀድሞ ያዘጋጀልንን በጎ ሃሳቡንና ፈቃዱን የምንኖርበትም ነው፡፡ በወጣትነት ሕይወታችን ውስጥ ስሜታችንን የሚይዙና ትኩረታችንንም የሚስቡ ብዙ ጉዳች ቢኖሩም ከእግአብሔር ጋር የምንኖረውን ክርስቲያናዊ ኑሯችንንና በፊቱም የምናድግበትን ጸጋ ተጠንቅቀን የምንይዘው እንጂ ቸል የምንለው አይደለም፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ የእለት ተእለት እንቅስቃሴያችን በጥንቃቄና በማስተዋል የምናደርገውና የምንፈጽመው እንጂ ቸል የምንለው ተራ ጉዳይ አይደለም፡፡ በሚያልፈው ምድራዊ ኑሯችን ወስጥ ለማያለፈው፤ ለሚበልጠውና ለማይፈጸመው ዘላለማዊ ሕይወት ራሳችንን እንደምናዘጋጅበት አንስተውም፡፡ “ትሄዱ ዘንድ ምድሪቱንም ለመውረስ ትገቡ ዘንድ ቸል አትበሉ።” ተብለናልና ለመንፈሳዊ ሕይወታችን የሚጠቅሙንን ማናቸውንም አይነት በጎ ምግባራትና መንፈሳዊ ተግባራት ሁሉ ቸል ልንል አይገባንም፡፡ ከዛሬ ድካማችንና አለመቻላችን ባሻገር በክርስቶስ ጸጋና ምሕረት የምንቀበለውን ሕይወት በተስፋና በትዕግስት እንጠብቃለን እንጂ ባለማመንና ተስፋ በመቁረጥ ራሳችንን አናደክምም፡፡ “ነገር ግን፥ የኀይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይኾን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ በዅሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቈርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ዅል ጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን። የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የኾን ከኢየሱስ የተነሣ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለንና። ስለዚህ፥ ሞቱ በእኛ፥ ሕይወቱም በእናንተ ይሠራል።” 2ኛ ቆሮ 4፣7-12፡፡
    ምን እናድርግ ?
በምድር ላይ የምንኖው ይህ ሕይወታችን የእኛ ሳይሆን የክርስቶስ መሆኑን ተረድተን ወጣትነታችንን ለፈቃዱና ለሐሳቡ እንቀድስ፡፡ ክርስቲያናዊ ሕይወታችንም በአንድ ጊዜ የምንደርስበትና የምንፈጽመው ሳይሆን የእግዚአብሔርን ጸጋ አጋዥ በማድረግ ቀስ በቀስ የምናድግበትና የምንጠነክርበት ረጅም ሒደት በመሆኑ ለዚህ የተቀደሰ ሕይወት በየእለቱ ራሳችንን አናለማምድ፡፡ “ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ዅሉ እያሳያችኹ በእምነታችኹ በጎነትን ጨምሩ፥ በበጎነትም ዕውቀትን፥ በዕውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ። እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ኾነው ቢበዙ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዕውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትኾኑ ያደርጓችዃልና፤ እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፥ የቀደመውንም ኀጢአቱን መንጻት ረስቷል። ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችኹንና መመረጣችኹን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉምና። 2ኛ ጴጥ 1፣5-10::  

Monday, April 25, 2016

›‹›‹››‹›‹››‹›‹››‹ሰሙነ ሕማማት ‹;‹;››‹›‹›››;›፡›፡›

በነቢዩ ኢሳይያስ «ነስአ ደዌነ ወፆረ ሕማመነ፤ በእውነት ደዌአችንን ተቀበለ፣ ሕመማችንንም ተሸከመ፣ እኛ ግን እንደተመታ፣ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሰፈ፣ እንደተቸገረም ቆጠርነው፡፡ እርሱ ግን ስለመተላለፋችን ቆሰለ፣ ስለ በደላችንም ደቀቀ፣ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፣ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን፡፡» /ኢሳ. 53፣4-7/ ተብሎ የተነገረው ቃል ተፈጽሞ፣ ጌታችን ለድኅነተ ዓለም ሲል በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የተቀበለው ጸዋትወ መከራ የሚዘከርበት ሳምንት ነው፡፡ ከሆሣዕና ማግስት እስከ ትንሣኤ ያለው የጾመ እግዚእነ መዝጊያ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡
በሰሙነ ሕማማት ካህናትና ምእመናን በአጸደ ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው፣ ከሐሜት፣ ከነገርና ከኃጢአት ርቀው፤ የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ ሲያዜሙ፣ ግብረ ሕማም በመባል የሚታወቀውን መጽሐፍ ሲያነቡ፣ ሲሰሙ፣ ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፡፡ ካህናትና ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፣ በሠለስት፣ በስድስት፣ በተሰዓት /በዘጠኝ/ ሰዓት፣ በሰርክ /በዐሥራ አንድ/ ሰዓት መላልሰው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፣ በተለይም ካህናት በማንኛውም አገልግሎት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፣ ምክንያቱም ጌታችን የደረሰበትን መከራ ሥቃይን እና 5ሺ 5መቶ ዘመን የሰው ልጅ በጨለማ ግዞት ይኖር እንደነበር ለማዘከር ነው፡፡ ሰሙነ ሕማማት የጌታችንን ሕማማት ከማሰብ ጋር በርካታ ድርጊቶች መፈጸማቸውንም የምናስታውስበት ሳም ንት ነው፡፡ በዕለት በዕለት ከፍለን በየትኛው ቀን ምን ተደረገ እያልን እንጠይቅ?

›‹›‹›‹›‹››‹›‹›‹››‹‹›‹›‹›››‹›‹ሰኞ፡-
ጌታችን የሆሣዕና ዕለት ቢታንያ በምትባል መንደር ያድራል በማግስቱም ከቢታንያ ሲወጣ ተራበ /ማር. 11፣11-14/ ቅጠል ያላትን በለስ ከሩቅ አይቶ ወደ በለሲቱ ቀረበ፣ ነገር ግን ከቅጠል በቀር አንዳች ፍሬ አላገኘባትም፡፡ ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ብሎ ረገማት፡፡ በዚህ ምክንያት ይህ ዕለት መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል፡፡

ትርጓሜ፤ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ናት፤ ፍሬ የተባለች፣ ሃይማኖትና ምግባር ናት፡፡ ከእስራኤል ፍቅርን፣ ሃይማኖትን፣ ምግባርን ፈለገ አላገኘም፡፡ እስራኤልን ሕዝበ እግዚአብሔር መባልን እንጂ፣ ነቢይነት፣ ካህንነት፣ መሥዋዕት አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፡፡ በመርገሙ ምክንያት ትንቢት ክህነት መሥዋዕት ከቤተ እስራኤል ጠፉ፡፡

በለስ ኦሪት ናት፡- ኦሪትን በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት ኦሪትና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ በማለት ፈጸማት፤ ሕገ ኦሪትን ከመፈጸም በቀር በእርሷ ድኅነት አላደረገባትምና ፍሬ ባንቺ አይሁን አላት፤ ድኅነት በአንቺ አይደረግብሽ ብሏታልና እንደመድረቅ ፈጥና አለፈች፡፡ በአዲስ ኪዳን የድኅነት ዘመንም ተተካች፡፡

በለስ ኃጢአት ናት፡፡ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነች ሁሉ ኃጢአት በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢአትም ሲሠሩት ደስ ደስ ያሰኛል ኋላ ግን ያሳዝናል፡፡ በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚለውም፤ በኃጢአት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ለማለት ነው፡፡ በለሷም ስትረገም ፈጥና መድረቋ፣ በአዳም ምክንያት ያገኘችን ዕዳ በደል በእርሱ እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡

ከዚህ ቀጥሎ ወደ ቤተ መቅደስ ሔደ፤ ቤተ መቅደስ ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምሥያጥ /የንግድ ቤት/ ሆኖ ቢያገኘው፤ «ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች... እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት» ማቴ.21፣13 ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸዉ፣ ገርፎም አስወጣቸዉ፣ ይህም የሚያሳየዉ ማደሪያው ቤቱ የነበርን እኛ የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ አንጽሖተ ቤተ መቅደስ የተፈጸመበት ሰኞም ይባላል፡፡


 ‹››‹›‹›‹›‹››‹›‹›‹›››‹›‹›‹ማክሰኞ፡-

ሰኞ ባደረገው አንጽሖተ ቤተመቅደስ ምክንያት፣ ሹመትን ወይም ሥልጣንን ለሰው ልጅ የሰጠ ጌታችን፣ ስለ ሥልጣኑ በጸሐፍት ፈሪሳውያን ተጠይቋልና፤ የጥያቄ ቀን ይባላል፡፡

ጥያቄውም ከምድራውያን ነገሥታት፣ ከሌዋውያን ካህናት ያይደለህ ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን፣ በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? የሚል ነበር፡፡ /ማቴ. 21፣23-27፣ ማር. 11፣7-35፣ ሉቃ. 21፣23-27፣ ማር. 11፣27-33፣ ሉቃ. 20፣1-8/፤ እርሱም ሲመልስ፤ «እኔም አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ፣ እናንተም ብትነግሩኝ በማን ሥልጣን እነዚህን እዳደርግ እነግራችኋለሁ፡፡ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረ፣ ከሰማይን? ወይስ ከሰዉ? በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ ወይስ በሰው ፈቃድ?» አላቸው፡፡ እነርሱም ከሰማይ ብንል ለምን አልተቀበላችሁትም ይለናል፤ ከሰው ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን እንደ አባት ያከብሩታል፣ እንደ መምህርነቱ ይፈሩታልና ሕዝቡን እንፈራለን፤ ተባብለው ከወዴት እንደሆነ አናውቅም ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም አላቸው» ይህንንም መጠየቃቸው እርሱ የሚያደርጋቸውን ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተዉት አልነበረም፣ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ እንጂ፡፡

በማቴ. 21፣28፣ ምዕ. 25፣46፣ ማር. 12፣2፣ ምዕ. 13፣37፣ ሉቃ. 20፣9፣ ምዕ. 21፣38 የሚገኙት ትምህርቶች ሁሉም የማክሰኞ ትምህርት ይባላሉ፡፡ በዚህ ዕለት በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረ፣ የትምህርት ቀንም ይባላል፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ከሥጋዊ ነገር ርቆ በዚህ ሰሞን የሃይማኖት ትምህርት ሲማር ሲጠይቅ  መሰንበቱ መጽሐፋዊ ሥርዓት ነው፡፡

‹›‹››‹›››‹›‹››‹‹;‹›‹;›‹›‹›‹›››‹›‹ረቡዕ፡-
ምክረ አይሁድ ይባላል፡፡ ምክንያቱም የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው ምክር ያጠናቀቁበት ቀን ነውና፡፡ በዚህ ምክራቸው ላይ በጣም ትልቅ ጭንቀት ነበር፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት ቀን የተቃረበ በመሆኑ፣ ብዙው ሕዝብም በጌታችን ትምህርት የተማረኩ፣ ተአምራቱንም የሚያደንቁ ስለ ነበር ሁከት እንዳይፈጠር ነው፡፡ በዚህ ጭንቀት ሳሉ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ፣ በመካከላቸው በመገኘት የምክራቸው ተባባሪ ሆኖ ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል፡፡ /ማቴ. 26፣1-14፣ ማር. 14፣1-2፣ ቁ 10፣11፣ ሉቃ. 22፣1-6/፤ የሐዲስ ኪዳን ካህናትና ምእመናን በዚሁ ዕለት በቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው መላ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔር አስገዝተው የሞት ፍርዱን በማሰብና በማልቀስ፣ ሐዋርያት ከጌታችን መያዝ በኋላ በኀዘን በፍርሐት እንደነበሩ እያሰቡ መጻሕፍትን በማንበብ በጾም፣ በጸሎ ትና በስግደት ተወስነው ይቆዩና ከአሥራ ሁለት ሰዓት በኋላ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡

የመልካም መዓዛ ቀንም ይባላል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን በዚህ ዕለት በቤተ ስምዖን ዘለምጽ ተቀምጦ ሳለ፣ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት፣ /ባለሽቱዋ ማርያም/፤ «ከእንግዲህ ወዲህ በኃጢአት ተበላሽቶ ይኖር የነበረውን ሕይወቴን እንደዚህ መልካም ሽቱ የሚያጣፍጥ፣ ኃጢአትን ይቅር የሚል አምላክ መጣ» ስትል ዋጋው እጅግ በጣም ውድ የሆነ፣ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ የሚያወጣ፣ በአልባስጥሮስ ብልቃጥ የተሞላ ሽቱ ይዛ በመሔድ በጠጉሩ /በራሱ/ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባችው ነው፡፡ ረቡዕ የመዓዛ ቀን የተባለው፡፡

ረቡዕ የእንባ ቀንም ይባላል፡፡ ማርያም እንተ እፍረት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ፣ መላ ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት በእንባዋ እግሩን አጥባዋለችና፤ በጠጉሯም በእንባዋ ያጠበችውን እግሩን አብሳዋለችና፡፡ /ማቴ. 26፣6-13፣ ማር. 14፣.9፣ ዮሐ. 12፣8/ ኃጢአትን በማሰብ ማልቀስና ራስን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ማቅረብን ከምታስተምረን ማርያም እንተ እፍረት እንባን ለንስሐ ሕይወት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

‹›‹››‹›‹›‹›‹››‹›‹›‹›‹››‹›‹››‹ሐሙስ፡-
በቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ስያሜዎች ያሏቸው በርካታ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ዕለት ነው፡፡

ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፡፡ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደ አምላክ፣ መሆኑን ለመግለጥና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ያደረበት ነውና ጸሎተ ሐሙስ ተባለ፡፡ /ማቴ. 26፣36-46 ዮሐ. 17/፡፡

ሕፅበተ ሐሙስ ይባላል፡፡ ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ይህም የሚያሳየው የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳትና የደብር አስተዳዳሪዎች፤ «በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ እኛም የአንተን አርአያ አንዘነጋም የሌላውን እግር እናጥባለን፤» ሲሉ በቤተ ክርስቲያን የተገኙትን ምእመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡

የምስጢር ቀን ይባላል፡፡ ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ በዚህ ዕለት ተመሥርቷልና፡፡ ይኸውም «ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ ብሉ» ጽዋውንም አንስቶ አመሰገነ «ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱም ጠጡ» በማለት፤ እኛ ከእርሱ ጋር፣ እርሱ ከእኛ ጋር አንድ የምንሆንበትን ምስጢር ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ፣ ለደቀመዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ሥያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል ይዘጋጃል፡፡

የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡፡ ምክንያቱም መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ «ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን ሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱ ጠጡ» በማለቱ ይታወቃል /ሉቃ. 22፣20/ ኪዳን ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ስለሆነ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ተባለ፡፡

የነጻነት ሐሙስ ይባላል፡፡ ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ፣ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ጌታችን ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር «ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም ባርያ ጌታዉ የሚያደርገውን አያውቅምና ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ» በማለት /ዮሐ. 15፣15/፤ ከባርነት የወጣንበት ልጆች የተባል በትን ቀን የምናስብበት በመሆኑ ሊቃውንቱ የነጻነት ሐሙስ አሉት፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያንም ከኃጢአት ባርነት ርቆ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት  ሕይወቱን መምራት ይኖርባታል፡፡ ባሮች አልላችሁም ተብለናልና፡፡

የጸሎተ ሐሙስ ምስጢራት በብሉይ ኪዳን

ለፋሲካ ዝግጅት ተደርጎበታል፡፡ ዝግጅቱም በሦስቱ ወንጌላት ላይ ተመዝግቧል /ማቴ. 26.7-13/፡፡ ፋሲካ ማለት ማለፍ ማለት ነው፡፡ ይኸውም እስራኤላውያን በግብፅ ምድር ሳሉ መልአኩን ልኮ እያንዳንዱ እስራኤላዊ የበግ ጠቦት እንዲያርድና ደሙን በበሩ ወይም በመቃኑ እንዲቀባ ለሙሴ ነገረው፡፡ ሙሴም ለሕዝቡ ነገረ፣ ሁሉም እንደታዘዙት ፈጸሙ፡፡ መቅሰፍት ከእግዚአብሔር ታዞ መልአኩ የደም ምልክት የሌለበትን የግብፃውያንን ቤት በሞተ በኲር ሲመታ፣ የበጉ ደም ምልክት ያለበትን የእስራኤላውያንን ቤት ምልክቱን እያየ ማለፉን ለማመልከት ነው፡፡ /ዘጸ. 12፣1-20/፡፡ በዚህ መነሻነት በየዓመቱ እስራኤላውያን በመጀመሪያ ወራቸው በ14ኛው ቀን በግ እያረዱ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ፡፡ ሀገራችንም አስቀድማ ብሉይ ኪዳንን የተቀበለች ሀገር እንደመሆኗ ይህ ድርጊት ይፈጸምባት ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳንም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ፋሲካ ተብሎ የተጠራበት ምክንያት በዚህ በፋሲካ በዓል ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ደሙን ስላፈሰሰልን ነው፡፡ በደሙ መፍሰስ ሞተ በኲር የተባለ ሞተ ነፍስ ርቆልናልና፡፡ «ፋሲካችንም ክርስቶስ ነው» /1ቆሮ. 5፣7 1ጴጥ. 1፣18-19/

በዚህ ዕለት እንደ ማክሰኞ ሁሉ በዮሐ. 14፣16 የሚገኘውን ለደቀመዛሙርቱ ረጅም ትምህርት አስተምሯል፡፡ የትምህርቱም ዋና ዋና ክፍሎች ምስጢረ ሥላሴ የሦስትነት ትምህርት፣ ምስጢረ ሥጋዌ /የአምላክ ሰው መሆን/፣ ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን /የዳግም ምጽአቱን ነገር/ ነው፡፡ እነዚህን ትምህርቶች በስፋትና በጥልቀት መማር እንደሚገባ ሲያስረዳ፣ በተአምራት ሊገልጥላቸው ሲችል በረጅም ትምህርት እንዲረዱት አድርጓል፡፡ ደቀ መዛሙርቱም እሱ እያስተማራቸው ሳለ ያልገባቸውንም እየጠየቁ ተረድ ተዋል፡፡ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ተገኝተን መማርና ያልገባንን ጠይቆ መረዳት እንደሚገባን እንማራለን፡፡ በዚሁ ዕለት ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ የሰጠበት ቀን ነው፡፡ ማቴ. 26፣47-58

‹››‹››‹›‹›‹›‹››‹›‹›‹›‹›‹›‹›››ዓርብ-

የስቅለት ዓርብ ይባላል፡፡ የዓለም ሁሉ መድኃኒት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ መዋሉን ለማስታወስ ነው፡፡ /ማቴ. 27፣35/፡፡

መልካሙ ዓርብ ይባላል፡፡ ይህም የሚያስገነዝበን ከስቅለተ ክርስቶስ በፊት አንድ ሰው ሲያጠፋ ተሰቅሎ ይሞታል፡፡ በሮማውያን ሕግ መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት ነበር፡፡ በዚህ ዕለት የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል ጌታችን በደሙ ቀድሶ የምሕረት ምልክት፣ የሕይወት አርማ፣ የዲያብሎስ ድል መንሻ ስለ አደረገው፣ በሞቱ መልካሙን ሕይወትን ስለአገኘን መልካሙ ዓርብ ተብሏል፡፡

የትንሣኤን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም የሚሔዱ ምእመናን ሁሉ በዕለተ ዓርብ መከራውን ለማሰብ ከቤተ ጲላጦስ እስከ ጎልጎታ መቃብረ ክርስቶስ ድረስ ጉዞ ያደርጋሉ፡፡ ጉዞ የሚደረግባቸውም አሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል የተፈጸሙባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡

በዚህ ዕለት በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው መከራውን በማሰብ ሲሰግዱ የሚውሉ እንዳሉ ሁሉ፤ በአንጻሩ ደግሞ በስም ክርስቲያን ተብለን ከምንጠራው መካከል፣ ተድላ ደስታ በሚፈጸምባ ቸው ሥፍራዎች ክፉ ሥራ ስንፈጽም የምንውል አንጠፋም፡፡ እንዲህ የምናደርግ ሁሉ በአለፈው ልንጸጸትና በቀሪ ዘመናችን ልንታረም ይገባል፡፡ በዓመት አንዴ የምናገኘው ይህ ዕለት ቀራንዮን የምናስብበት፤ ነገረ መስቀሉን የምናስተውልበት እንጂ ስለ ምድራዊ ኑሮአችን ስንባክን ኃጢአት ስንሠራ የምንውልበት ሊሆን አይገባም፡፡

›‹›‹›‹››‹›‹›‹›‹››‹›‹›‹›‹›‹››‹›‹ቅዳሜ-

ቀዳም ሥዑር ይባላል፡፡ በዚች ዕለት ከድሮው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምት ውል የተሻረችው ቅዳሜ ተብላለች፡፡

ለምለም ቅዳሜ ካህናቱ ለምእመ ናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት ስለሆነ በዚህ ተሠይሟል፡፡ ቀጤ ማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል፡፡

ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል፡፡ ቅዱስ ቅዳሜ መባሉ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው  ሁሉ ያረፈበት ሲሆን፤ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን  ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ፣ በነፍሱ ሲዖልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷ ታል፡፡ በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘ ለዓለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ከሌሎቹ ዕለታት የተለየ ዕለት ለማለት ቅዱስ ቅዳሜ ተብሏል፡፡ የዕለታ ቱን ክብርና ሥያሜ ከማወቅና ከመ ረዳት ጋር በዕለታቱ የታዘዙትን ሃይማኖታዊ ግዴታዎችን መወጣት ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡
ምንጭ- መጽሐፈ ግብረ ሕማማት

-ሐመርና መለከት መጽሔቶች

Friday, April 18, 2014



                እንኳን ለጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

                                         በዓሉ የሰላም የፍቅር የበረከት ይሁንላችሁ


Thursday, April 17, 2014

“እንበለ ደዌ ወህማም ወእንበለ ጻዕር ወድካም አመከመዮም               ያብጽሀነ ያብጽሀክሙ እግዚአብሔር በሰላም”

   እንኳን ለጸሎተ ሐሙስ /ሕጽበተ ሐሙስ/አረንጓዴ ሐሙስ 

                        በሰላም አደረሳችሁ 


Wednesday, April 16, 2014



   የመንዝ መ/ሜዳ ደ/ም/ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል 
                  ሰ/ት/ቤት 
         የተመሰረተበትን 32 ኛ ዓመት 
                  ለማክበር በዝግጅት ላይ ይገኛል




                       እንኳን ለሰሞነ ህማማት በሰላም አደረሳችሁ
       የቀድሞው የመንዝ መሐል ሜዳ ካቴድራል ሰ/ትቤት ማህበረ በኩር የቅዱስ ሚካዔል የጽዋ ማህበር ስለ ማህበሩ መስፋፋትና መጠናከር ለመወያየት ሚያዚያ 13 /08/2006 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሠዓት ስብሰባ ለማድረግ ፕሮግራም ይዟል፡፡ በዚህ እለት የማህበሩ አባላትም ሆናችሁ አባል ለመሆን የምትፈልጉ በመ/ሜዳ/ደ/ም/ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ህጻናት ማሳደጊ አዳራሽ ተገኝታችሁ የፕሮግራሙ ተካፋይ እንድትሆኑ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
        ለበለጠ መረጃ፡-  092085 3929
                       ፡- 0923469749    
        
 በኢሜል አድራሻችን  mehalmedamicaeal@gmail.com         በፌስቡክ አድራሻችን https://www.facebook.com/menzmehalmedamicaeal?ref=hl

Friday, April 11, 2014



     የነደያነን ምገባ ለትንሳኤ በአል በሰ/ት/ቤቱ ከምእመኑ ገንዘብ እና እንጀራ          በመለመን በየአመቱ የሚካሄድ ትልቅና ነፍስን የሚያስደስት የበረከት ስራ